`

[ታደሠ በላይ ፤ ሠ ቆጣ የካቲት 18 ፥ 2016 ዓ.ም]

ብጹዕ አቡነ በርናባስ የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ድጋፍ ጥሪ አሳሳቢነት እና በዋግ ልማት ማህበር (ዋልማ) አስተባባሪነት በተሰበሰበ ከ 3.9 ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብ ድጋፍ የተገዛ 900 ኩንታል ማሽላ በሠሀላ ሰየምት ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ። የገንዘቡ ድጋፉ የተገኘውም፦

  • 3,320,606.00 ብር በወ/ሮ ሰብለ አበራ በየነ አሰተባባሪነት፤ በእንግሊዝ-ለንደን ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን፣
  • 336,875.00 ብር በቀሲስ ዘውዱ ግርማ አሰተባባሪነት፤ በእንግሊዝ፤ በስፔን-ማድሪድ እና አዲስ አበባ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣
  • 252,400.00 ብር ከካሳ እና ደስታ ቤተሰብ፤ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ እና በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የቤተሰቡ አባላት ነው።

ብፁዕ አቡነ በርናባስ የተደረገውን የአስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ጥሪ ተቀብለው የገንዘብ ድጋፉን ላስተባበሩት እና ድጋፉን ላደረጉ ወገኖች በሙሉ አመስግነዋል። በቀጣይም ለእንሰሳት መኖ፣ የውኃ ማጠራቀሚያ እና መሰል ድጋፎች እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። የዋግ ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር ኃይሌ ወልዴ የድጋፍ ጥሪውን ላደረጉት ብፁዕ አቡነ በርናባስ እና ጥሪያቸውን ተከትለው ድጋፉን ላስተባበሩ እና ድጋፍ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። በዚህም በድምሩ ከ 3.9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብ ድጋፍ የተገኘ ሲሆን 900 ኩንታል ማሽላ ተገዝቶ ለድርቅ ተጋላጭ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። አክለውም የዛሬው ድጋፍ ልዩ የሚያደርገው ከወገኖቻችን የተገኘው ገንዘብ በልማት ማኅበራችን አካውንት ቀጥታ ገቢ ሆኖ የድጋፍ እህሉ የተገዛ መሆኑንም አስረድተዋል። የሠሀላ ሠየምት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ብሩ አባታችን የመንገድ ርቀት ሳይገድበዎ ችግራችንን ለመረዳትና ለማየት ድጋፉን ይዘው በወረዳችን በመገኘትዎ በወረዳው ህዝብ እናመሰግናለን ብለዋል:: በቸገረን ጊዜ ሁሉ ሃይማኖት እና ብሔር ሳይለዩ ስንራብ አብልተው፣ ስንጠማ አጠጥተው ከዚህ ያደረሱን አባታችን ናቸው ብለዋል። አክለውም ብፁዕ አቡነ በርናባስ በዞኑ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ባደረጉት ጥሪ በተገኘው ከ3.9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 900 ኩንታል ድጋፍ መደረጉን በመግለፅ የወገኖቻችን ችግር የእኛ ችግር ነው ብላችሁ ላደረጋችሁት ድጋፍ በወረዳው ህዝብ ስም አመሰግናለሁ ብለዋል። ወ/ሮ ባየች ማሩ የወረዳው ነዋሪ ናቸው፤ 4 ቤተሰባቸውን እናትም አባትም ሆነው እንደሚያስተዳድሩ አስረድተው፣ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል። ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ዘለቄታዊ ባይሆንም ጊዜያዊ ችግራቸውን እንደሚቀርፍላቸው ገልፀዋል።

ህብረት ለዋግ ልማት!

Categories : Categories : Partners & Supporters

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *