[ታኅሳስ 10 ፥ 2016 ዓ.ም]
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በዋግ ኽምራ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ። የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ከተለያዩ ቅርንጫፎቹ ያሰባሰበውን ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በዋግኽምራ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉን ከቃሊቲ ፣ ከጅግጅጋ፣ ከሞያሌ፣ ከሀዋሳ እና ጅማ ያሰባሰበው ኮሚሽኑ በራሱ ትራንስፖርት ድጋፉን አከማችቶ ለማድረስ ማዕከል ወደ ሆነው አዳማ በማጓጓዝ ለዋግ ልማት ማኅበር (ዋልማ) ጊዜያዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል። የዋግ ልማት ማኅበር የቦርድ አባል እና በአዲስ አበባ የጊዜያዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ምትኩ በየነ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ እና ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሲደግፍ መቆየቱንም ተናግረዋል። የዛሬው ድጋፍ ለ4ኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በወገኖች ስም እናመሰግናለን ብለዋል። የተሰበሰቡት የዕለት ደራሽ ምግቦች እና አልባሳት በፍጥነት ወደቦታው እንደሚጓጓዙም ተናግረዋል። ድጋፉን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ እና ምክትል ኮሚሽነር ምስራቅ ማሞ በአዳማ ተገኝተው አስረክበዋል። ኮሚሽነሩ ከዚህ ቀደም ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው ሌሎችም ተመሳሳይ እና ፈጣን የድጋፍ እጃቸውን መዘርጋት አለባቸው ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል። ለተጨማሪ መረጃ የአሚኮን ዘገባ እዚህ ይመልከቱ።
ዋልማን በሃሳብዎ፣ በእውቀትዎ፣ በገንዘብዎ ይርዱ !