ሰቆጣ 21/03/2015ዓ.ም
ISEE የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በዋግ ልማት ማህበር አስተባባሪነት የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። መሰረቱን በኔዘርላንድስ ሃገር ያደረገ Interkerkelijke Stichting Ethiopië/Eritrea (ISEE) የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በዋግ ልማት ማህበር አስተባባሪነት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል በድሀና ወረዳ ለጭላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሆን 711,833.72 ብር ወጭ የተደረገባቸው 140 የተማሪዎች ኮንባይን ዴስክ ፣ 5 የመምህራን ጠረጴዛ፣ 10 መቀመጫ ወንበር ፣ 1 ዲስክቶፕ ኮንፒውተር እና 1 ፕሪንተር ድጋፍ አድርጓል።
የዋግ ልማት ማኅበር ም/ዳይሬክተር የገቢ ማስገኛ ተቋማት ሰራ አስኪያጅ ሙላው ደምሴ ለተደረገው ድጋፍ ISEEን አመስግነው፤ ዋግ በጦርነቱ በሁሉም ዘርፍ በሁሉም ወረዳዎች ሰፊ ጉዳትና ውድመት ደርሶል። በመሆኑ ሁሉም መንግስታዊ ፣መንግስታዊ ያልሆነም ተቋማት ፣ እንዲሁም ሃገር በቀል የሆኑና በውጭ የሚገኙ ግብረሰናያ ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲደግፉ ጠይቀዋል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ ዋና ሃላፊ አቶ ሰይፉ ሞገስ ዞናችን ከጦርነቱም በፊት ሰፊ የትምህርት ግብአት ችግር የነበረበት ሲሆን ጦርነቱ ሲጨመርበት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖብናል” ሲሉ ገልፀው፤ ISEE ላደረገወ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ ችግሩ ሰፊ በመሆኑ ሁሉም መንግስታዊ ፣መንግስታዊ ያልሆነም ተቋማት ፣ እንዲሁም ሃገር በቀል የሆኑና በውጭ የሚገኙ ግብረሰናያ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።የወረዳው ም/አስተዳዳሪ እና የወረዳው የግብርና ልማት ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘነበ ማሞ እንደተናገሩት ዋልማ ከዚህ በፊትበ በት/ቤት ግንባታ በማተሪያል ድጋፍ በወረዳችን በርካታ ስራዎችን አከናውኗል እያከናወነም ነው ብለዋል። ኃላፊው አክለውም ዋልማ ለጭላ አጠ/1ኛ ደረጃ ት/ቤት የተለያዩ ግባዓቶች ድጋፍ በማረጉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አጋዥ በመሆኑ በወረዳው ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል። የጭላ ጉድኝት ማዕከል ሱፐርቫይዘን የሆኑት ንጉስ ሰፊው በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በመውደማቸው ተማሪዎች በአፈር እና በድንጋይ ላይ ተቀምጠው በአስቸጋሪ ሀኔታ እየተማሩ መቆየታቸውን አስታውሰው ዋልማ የተለያዩ ድጋፉችን በማደረጉ ተማሪዎች በምቹ ሁኔታ ተምረው ጥሩ ውጤት ለማምጣት አጋዥ በመሆኑ ለማህበሩ ትልቅ ምስጋና አቅረበዋል ። የጭላ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ደባሽ ተፈሪ ሰለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤የዋልማ አባል መሆን የወዴታ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የልጆቻችን የህልውና ግዴታ ነው።ዋልማ በተግባር እንዳሳየን የዋልማ አባል በመሆን ግዴታችንን እንወጣ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
የዋግ ልማት ማኅበር ከ ISEE ለተደረገለት ድጋፍ እጅግ ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል።